Ads Here

ሰኞ 3 ኦገስት 2020

ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ለሥራ አጥ ወጣቶች በብድር ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ቫዮ አውቶሞቲቭ




በተለምዶ ባጃጅ እየተባሉ የሚጠሩትን ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ለሥራ አጥ ወጣቶች በብድር ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ቫዮ አውቶሞቲቭ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አስታወቁ፡፡ ሁለቱ ተቋማት ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የብድር አገልግሎት ለማቅረብ ቡና ባንክ በመስማማቱ፣ በአገር ውስጥ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥመው ቫዮ አውቶሞቢል ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎችን ለሥራ አጥ ወጣቶች ለማቅረብ ተስማምተዋል፡፡ በሁለቱ ኩባንያዎች ስምምነት መሠረት 75,000 ብር ቅድመ ክፍያው በብድር ለተሽከርካሪ አምራቹ ከተፈጸመ በኋላ፣ ቀሪው በ24 ወራት ውስጥ ይከፈላል ያሉት የቫዮ አውቶሞቢል የንግድና ግብይት ኃላፊ ወ/ሪት ሊዲያ ኪዳኔ ናቸው፡፡

ወ/ሪት ሊዲያ እንዳሉት ለባ ለሦስት እግር ተሽከርካሪው የሚፈጸመው አጠቃላይ ክፍያ 175,000 ብር ሲሆን፣ በየወሩ 4,956 ብር እየከፈሉ የተሽከርካሪ ባለቤት መሆን እንዲችሉ ለወጣቶች ዕድሉ ተመቻችቶላቸዋል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በአነስተኛ መነሻ ገንዘብ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማ በማንገብ ከኢኮኖሚ ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ግብ እንደያዘ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ ቫዮ አውቶሞቢል ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በዘረጋው የብድር ሥርዓት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር፣ በትራንስፖርት መስክ የሚታየውን እጥረት ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከዋና መስመሮች ወይም መንገዶች ውጪ በሚገኙ አካባቢዎችና መንደሮች ውስጥ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን በብዛት የሚጠቀም ነዋሪ እንዳለ፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያትም ሥራ አጥ ወጣቶችን በዘርፉ ለማሰማራት ጥሩ አጋጣሚ እንዳለ ወ/ሪት ሊዲያ ይገልጻሉ፡፡
ድርጅቱ በቀን እስከ 50 ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥም በመሆኑ፣ የገበያ ፍላጎቱ እያደገ ሲመጣ የማምረት አቅሙንም በዚያው ልክ ያሳድጋል ተብሏል፡፡ እስካሁን ከ2,000 በላይ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ለገበያ ማቅረብ ችሏል፡፡ የብድር ሥርዓቱም ቅድሚያ ለሚመጡ ቅድሚያውን በመስጠት የሚያስተናግድ አሠራር እንደሚከተል ሥራ አስኪያጇ ጠቅሰዋል፡፡
የብድር አገልግቶቹ ከመጀመሩ በፊት ተሽከርካሪዎች በብዛት ተመርተው መከማቸታቸው ሲገለጽ፣ የገበያው ፍላጎት ከተመረተውም በላይ ከሆነ ግን ተጨማሪ ማስፋፊያ ስለሚደረግ እጥረት እንደማይፈጠር ተገልጿል፡፡

ቫዮ አውቶሞቲቭ አዲስ አበባና ዙሪያዋን ጨምሮ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በድሬዳዋ፣ በጂማ፣ በአምቦና በሌሎችም ከተሞች በሚገኙ ወኪሎቹና በቡና ባንክ ቅርንጫፎች አማካይነት በተመቻቸው የብድር አገልግሎት መሠረት ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሥራ አስኪያጇ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ