Ads Here

ማክሰኞ 4 ኦገስት 2020

የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በደረሰ የሰው ህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ወንጀል የተጠረጠሩ ፍርድቤት ቀረቡ



የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 አ/ም በ10 ወረዳዎች በደረሰ የሰው ህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ወንጀል የተጠረጠሩ 1 ሺህ 168 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ 198 ሰዎች አዲስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆኑ፥ ከ10 በላይ የሆኑ ሰዎች በወቅቱ የህግ ማስከበር ስራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው በቁጥጥር ስር የዋሉ የጸጥታ አካላት ናቸው፡፡

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ/ም በምእራብ አሪሲ ዞን በአሪሲ ነገሌ እና ዶዶላ ከተማና ወረዳ፣ በሻሻመኔ፣ ኮፈሌ፣ አዳባ ፣ ዶዶላ፣ ሻላ፣ ቆሬ እና አሳሳ ወረዳዎች በተፈጠረ ሁከትና አመጽ በርካታ በሰው ላይ እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

በዚህ በተፈጸመ ወንጀል የተጠረጠሩ 970 ተጠርጣሪዎች ሃምሌ 13 ቀን በወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው የጠየቁት ዋስትና ለጊዜው ወድቅ ተደርጎ ለመርማሪ ፖሊስ የወደመና ጉዳት የደረሰ ንብረትን በባለሙያ ለማስገመት እና በሰው ላይ የደረሰውን ጉዳት የህክምና እንዲሁም ህይወታቸው ያለፉትን የአስከሬን ምርመራ እና የምስክሮችን ቃል ለመቀበል ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ፍርድ ቤቶቹ ለፖሊስ 14 ቀን መፍቀዳቸው ይታወሳል።

በዛሬው ቀጠሮ 970 አዲስ ተጠርጣሪዎች እና 198 ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስም ከላይ በተጠቀሱት ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ በተሰጠው 14 ቀን የተጨማሪ ጊዜ አዲስ የምርመራ ስራ ይፋ አድርጓል።

በዚህ ምርመራ በተፈጸመው ወንጀል 434ቱ ላይ የምስክር ቃል መቀበሉን ገልጾ በባለሙያ በተደረገ የጉዳት እና የወደሙ ንብረቶችን በተሰራ ግምት በ32 ሆቴሎች፣ 17 አልጋ ቤት፣ 113 መኖሪያ ቤት ተቃጥለዋል ነው ያለው ፖሊስ።

በተጨማሪ 37 ምግብ ቤቶች፣ 215 መኖሪያ ቤቶች፣ 9 ወፍጮ ቤት፣ 85 ሱቆች፣ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው ያለው መርማሪ ፖሊስ የተቃጠሉ ሱቆች ደግሞ 47 ናቸው ሲል አብራርቷል።

መርማሪ ፖሊስ 67 የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተሰባበሩ ሲሆን የተቃጠሉ 3 የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ይገኙበታል ብሏል።

በተጨማሪም 1 የሃይማኖት ተቋም፣ 2 የዱቄት ፋብሪካዎች፣ 2 የመጠጥ ማከፋፈያና 5 ፎቆች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

በተጨማሪም 15 የግል ተሽከርካሪዎች የተቃጠሉ ሲሆን፥ 16 ተሽከርካሪዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያለው መርማሪ ፖሊስ ።

16 የሰው ህይወት ሲያለፍ ከ60 በላይ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል ነው ያለው መርማሪ ፖሊስ፡፡

በተጨማሪ ምስክር ቃል ለመቀበል እና ተጨማሪ ማስረጃ ለመስብሰብ 14 ቀን ተጨማሪ ይሰጠኝ ያለ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ዋስትና ይፈቀድልን ሲሉ የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም የወረዳ ፍርድ ቤቶቹ የመርማሪ ፖሊስ መርመራ በጥሩ መከናወኑን በምርመራ መዝገቡ በማረጋገጥ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን ፈቅዷል።

እንዲሁም 189 አዳዲስ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት በቀረቡ ተጠርጣሪዎች ላይም ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ አጠናቆ እንዲቀርብ 14 ቀን ፈቅዷል።

በእለቱ በተፈጸመ ወንጀልን በአግባቡ የጸጥታ ማስከበር ስራቸውን አልተወጡም የተባሉ ከ10 በላይ የጸጥታ አካላት ላይም ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የተጠየቀውን 14 ቀን በመፍቀድ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለነሃሴ 11ቀን 2012 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ