በአዲስ አበባ ከተማ 102 ህገ-ወጥ ሽጉጦችና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች መያዙን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ጀይላን አብዲ እንደተናገሩት፤ በመዲናዋ በተለምዶ ኮልፌ 18 ማዞሪያ እና ሰሜን ማዘጋጃ’ በሚባሉ አካባቢዎች ተጠርጣሪው ግለሰብ በተከራይዋቸው ቤቶች ውስጥ ነው ህገወጥ መሳሪያዎቹ የተያዙት።
በተደረገው ፍተሻም 102 ሽጉጦች 399 ጥይቶችና ሌሎች በርካታ የጦር መሳሪያ እቃዎች መያዛቸው ታውቋል፡፡
ተጠርጣሪው በሰጡት ቃል መሳሪያዎቹ መነሻቸውን ሱዳን አድርገው በጎንደር በኩል አዲስ አበባ እንደገቡም የተናገሩ ሲሆን ግለሰቡ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው።
ህገወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ቤት በመከራየት ወንጀሉን እንደሚፈጽሙ ጠቅሰው፤ ከዚህ አንጻር አከራዮች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና በኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ድጋሜ ሁከት ለመቀስቀስ የሚጥሩ አካላት እንዳሉ አቶ ጀይላን ተናግረዋል።
እነዚህ አካላት በዋናነት ምስሎችን ‘በፎቶ ሾፕ’ በማቀናበርና ከለውጡ በፊት የተደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አሁን እንደተከናወኑ በማስመሰል ህዝብን እያደናገሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህን እኩይ ተግባር ሊገነዘብ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።መንግስት አገርን በሁከት ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በህግ ጥላ ስር የማዋሉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ጀይላን ተናግረዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ የዜጎችን ድህንነት ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑንም መግለፃቸውን ኢአ ዘግቧል።
ወጣቶችም በሀሰት መረጃ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በሚደረግ ሙከራ ሳይዘናጉ የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁም ጥሪ ቀርቧል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ