Ads Here

ሰኞ 3 ኦገስት 2020

ተቋርጦ የነበረው የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር ተጀመረ



የኢትዮጵያ ውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር አንዳስታወቀው ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት መሪነት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደርጉትን ድርድር ዛሬ ቀጥለዋል፡፡በህብረቱ ሲመራ የነበረው ድርድር መግባባት ላይ ሳይደረስ ነበር ከሁለት ሳምንታት በፊት የተቋረጠው፡፡ድርድሩ ከሳምንት በፊት ሊጀመር የነበረ ቢሆንም ሱዳን የአንድ ሳምንት ጊዜ እንዲሰጣት በመጠየቋ ምክንያት ዛሬ ሊጀመር እንደቻለ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

እንደሚኒስቴሩ መግለጫ ድርድሩ ለሚቀጥለው አንድ ሳምንት ይቀጥላል፡፡

ሚኒስቴሩ “የዚህ ሳምንቱ ድርድር ቀደም ሲል ከተካሄደው የ11 ቀናቱ ድርድር በኋላ ለመሪዎች በቀረበው ሰነድ መሠረት መሪዎቹ ባስቀመጠጡት አቅጣጫ የሚቀጥል” ነው ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ “ፍትሓዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ድርድሩን ለመቋጨት” እንደምትሰራም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት ማጠናቀቋንና በመጀመሪያ አመት 4.9 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ውሃ እንደያዘች ማስታወቋ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውሃ መሙላቷን ማጠናቀቋን ይፋ ከማድረጓ በፊት ግብጽና ሱዳን የውሃ ሙሌቱ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መሞላት እንደሌለበት ሲሞግቱ ቆይተው ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ የውሃ ድርሻ ተጠቅማ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ተጽእኖ ሳታሳድር ለልማት አለማ ግድብ መገንባቷ ተገቢ መሆኑን በተደጋጋሚ ስገልጽ ቆይታለች፡፡ ሱዳን የግድቡን መገንባት ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደማትቃወም ገልጻ፤ነገርግን አስተዳደሩና አሞላሉን በሚመለከት የሶስትዮች ስምምነት መኖር አለበት የሚል አቋም ስታንጸባርቅ ቆይታለች፡፡

ግብጽ በአንጻሩ በ1950ዎቹ በቅኝ ግዛት ወቅት የተፈረሙ ስምምነቶችን ጭምር በመጥቀስ ታሪካዊ የውሃ ድርሻየ ይቀንሳል የሚል አቤታቱ እያሰማች ነው፤የግድቡን መገንባትም ትቃወም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ግን ይህ ስምምንት እንደማይመለከታት ገልጻለች፡፡

በየካቲት ወር በዋሸንግተን ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በኢትዮጵያ ተቃውሞ ከተቋረጠ በኋላ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዲመራ ስምምነት ላይ ደርሰው፤ ድርድሩን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ