በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ቅዳሜ ዕለት ሦስት ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን አንድ የክልሉ ሠላም ግንባታና የጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።
አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ፣ የቤንሻንጉል ሠላም ግንባታና የጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ለቢቢሲ እንደገለጹት ታጣቂዎቹ ሦስት የጉባ አካባቢ ነዋሪዎችን እንደወሰዱና እስካሁን የት እንዳሉ አለመታወቁን ገልጸዋል።
እገታው የተፈጸመው ቅዳሜ ዕለት መሆኑን የሚናገሩት አቶ አብዱለዚዝ "ታጋቾቹ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት" ናቸው በማለት የደረሱበት ባለመታወቁ ቤተሰቦቻቸው ለአካባቢው ባለስልጣናት ማመልከታቸውን ገልጸዋል።
ታጋቾቹ የጉባ ወረዳ ነዋሪዎች ሲሆኑ ታጣቂዎቹ ያገቷቸውን ሰዎች ለመንግሥት መረጃ ትሰጣላችሁ ከማለት በተጨማሪ የቤተሰብ አባሎቻቸው ከአካባቢው መስተዳደሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመጥቀስ መታገታቸውን ቤተሰቦቻቸው እንደተናገሩ ኃላፊው ጠቅሰዋል።
የታገቱትን ሰዎች በተመለከተ "ስላሉበት ሁኔታ የታወቀ ነገር የለም። ስላሉበት ሁኔታ እርግጠኞች አይደለምን። ነገር ግን ተይዘው በተወሰዱበት አቅጣጫ የመከላከያ ሠራዊት ተሰማርቶ ታጣቂዎቹን ለመያዝና ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላም መከላከያ እና ልዩ ኃይል ታጣቂዎቹ ተደብቀውባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ላይ አሰሳ በማድረግ ጥቂት የማይባሉት እንደተገደሉ የተናገሩት አቶ አብዱላዚዝ "[ታጣቂዎቹ] ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ውስጥ ስለገቡ የቻሉትን ያህል ጥፋት መፈጸም ነው ፍላጎታቸው። ነገር ግን መውጫ የላቸውም. . . ሠራዊቱ ተሰማርቶ እያሰሰ ነው" ብለዋል።
ከሳምንት በፊት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በጉባ ወረዳ አቡጃር ቀበሌ ላይ ጥቃት ፈጽመው ቢያንስ 13 ሰዎች ተገድለው ሌሎች ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚታወስ ሲሆን የክልሉ ልዩ ኃይልና የአገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ታጣቂዎቹን ለመያዝ በከፈተው ዘመቻ በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውና መያዛቸው ተገልጿል።
ይህንንም በተመለከተ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ በተለይ እንደገለጹት ቀደም ባለው ጥቃት ውስጥ ተሳትፈው ከነበሩት ታጣቂዎች መካከል 13ቱ ሲገደሉ 30ዎቹ ደግሞ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።
በታጣቂዎቹ እርምጃ የተወሰደው በመከላከያና በክልሉ ልዩ ኃይል በጋራ በተከታታይ በተደረጉ ዘመቻዎች መሆኑን አስረድተዋል።
ጥቃት የደረሰባቸውን ሰላማዊ ሰዎችና ለፍቶ አዳሪ ዜጎች መሆናቸው የሚናገሩት ምክትል ኃላፊው "የታጠቁ ሽፍቶች" ሲሉ የገለጿቸው የጥቃት አድራሾቹ ዓላማ በአካባቢው ግጭት ማስነሳት መሆኑን ጠቁመዋል።
አካባቢው አሁን ሠላማዊ እንቅስቃሴው በተለመደው መልኩ መቀጠሉን ተናግረው "የቀሩትን ጥቃት አድራሾች አድኖ ለመያዝ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ ተበታተነው የሚገኙትን ሽፍቶች የመያዝ ሥራም እየተሠራ ነው" ብለዋል።
ቤንሻንጉ ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሌ ሀሰን ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ኢቢሲ እንደተናገሩት፣ ጥቃቱ የደረሰው በክልሉ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በሚፈልጉ ኃይሎች ድጋፍ የሚደረግላቸውና በሱዳን ድንበር አካባቢ ስልጠና ሲወስዱ በነበሩ ቡድኖች አማካኝነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፈጸሙት ግድያ በኋላ በነበሩ ቀናት በጸጥታ ኃይሎች በተከታታይ በተወሰዱ እርምጃዎች ከ70 በላይ የሚጠጉት መያዛቸውንም ጠቁመዋል።
ተያዙ ስለተባሉት ታጣቂዎች የቁጥር ልዩነትን በተመለከተ አቶ አብዱላዚዝ ሲናገሩ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም 30ዎቹ ከጥቃቱ ጋር ቀጥተኛ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተያያዘ ዜና በጉባ ወረዳ አልመሃል በሚባል ቦታ ሌላ ጥቃት ተፈጽሟል የሚል መረጃ እየወጣ መሆኑን የተጠየቁት አቶ አብዱላዚዝ "ችግር ተከሰተ የሚባለው ውሸት ነው። አጣርተን ትክክል አለመሆኑን ደርሰንበታል" በማለት በስጋት ከመኖሪያ ቦታቸው ሸሽተው የወጡ ሰዎች እንዳሉና የጸጥታ ኃይል ደርሶ በማረጋጋት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ኃላፊው አመልክተዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ከሐምሌ 20 ጥቃት በኋላ የአካባቢው አመራሮችን ጨምሮ "በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን" ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከክልሉና ከፌደራል መንግስት ከመጡ አመራሮች ጋር ከተደረገ ውይይት በኋላ ከኅብረተሰቡ የተሰጡ ጥቆማዎችን መሠረት አድርጎ ብዙዎች መያዛቸውን አስታውቀዋል።
አካባቢው አሁን ሠላማዊ መሆኑን ጠቁመው ቤታቸው ትተው የሸሹ ሰዎችም ንብረታቸውን እያወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
አልመሃል አካባቢ ጥቃት ስለመድረሱ እና ታጣቂዎች ስለመያዛቸው ግን የሰሙት ነገሩ አለመኖሩን ጠቁመው ታጣቂዎቹ ከቦታ ቦታ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኝ ሲሆን ከሱዳን ጋር የሚካለል አካባቢ ነው። በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ በሚፈጸም ጥቃት በርካታ ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም አጋጥሟል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ