Ads Here

ረቡዕ 5 ኦገስት 2020

የማክሰኞው የአቶ በቀለ ገርባ እና የአቶ ደጀኔ ጣፋ የፍርድ ቤት ውሎ



የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ላይ ቀዳሚ የምርመራ መዝገብ መከፈቱን አቃቤ ሕግ እና መርማሪ ፖሊስ አስታውቋል።


መርማሪ ፖሊስ ፍርድ ቤት የሰጠውን ተጨማሪ 8 የምርመራ ቀናት ተጠቅሞ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ የተለያዩ ምርመራዎችን ሲያደርግ ቆይቶ የምርመራ ስራውን ማጠናቀቁን ለአራዳው ምድብ ችሎት አስታውቋል።

መርማሪ ፖሊስ፤ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ እንዲሁም በሻሸመኔ አከባቢ በተፈጠረው ሁከት በትራንስፖርት ዘርፉ ብቻ 37 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከትራንስፖርት ሚንስቴር አግኝቻለሁ ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የ32 ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ 110 ሆቴሎች፣ 239 መኖሪያ ቤቶች፣ 56 ሱቆች እና 82 የመንግሥት እና የግል ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን መርማሪ ፖሊስ አስረድቷል።

ከዚህ ሁከት ጀርባ የአቶ በቀለ ገርባ እጅ እንዳለበት ያመላከተ ሲሆን፤ በዚህም መርማሪ ፖሊስ ይህ የምርመራ መዝገብ ተዘግቶ አቃቤ ሕግ የከፈተው የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ይቀጥል ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የቀዳሚ ምርመራ መዝገቡ መከፈቱን ገልጿል።

የአቶ በቀለ ጠበቃዎች በበኩላቸው ፖሊስ ከዚህ ቀደም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ በማለት የፍርድ ሂደቱን ሲያጓትት እንደነበረው ሁሉ አሁንም ‘ቀዳሚ የምርመራ መዝገብ’ ከፍትኩ የሚለው አሁንም የፍርድ ሂደቱን ለማዘግየት ነው ብለው ተከራክረዋል።

ጠበቃዎቹ፤ ደንበኛቸው የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን አስክሬን በኃይል ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ስለማድረጋቸው እንዲሁም ሁከት እንዲነሳ ወደ ሻሸመኔ ስልክ ስለመደወላቸው የሚያመላክት ምንም አይነት ማስረጃ አልቀረበም ብለዋል።

አቶ በቀለ፤ ተጠርጥረው በቁጥጥር የዋሉበት ጉዳይ የዋስትና መብታቸውን እንደማያስከለክል በመናገር ‘የዋስትና መብቴ ይከበር’ ሲሉ ተናግረዋል። አቶ በቀለ ገርባ “እኔ የፖለቲካ ሰው እንጂ እና ጦር የማሰማራ ሰው አይደለሁም” በማለት በተፈጠረው ሁከት ተሳትፎ እንደሌላቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ የዋስትን መብት ጥያቄውን በተመለከት ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 30 2012 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የአቶ ደጀኔ ጣፋ የፍርድ ቤት ውሎ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጸሐፊ የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋም በተመሳሳይ ትናንት [ማክሰኞ] ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸዋል።

መርማሪ ፖሊስ የሰው እና የጽሑፍ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ምርመራ አላጠናቀቅኩም በማለቱ ለሐምሌ 30 2012 ዓ.ም. ተቀጥረዋል።

የአቶ ደጀኔ ጠበቃ የሆኑት አቶ ደጀኔ ፍቃዱ በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ምክንያቶች የደንበኛቸውን የፍርድ ሂደት እያጓተት መሆኑን በመጥቀስ ችሎት ፊት መከራከራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ደንበኛቸው የቀረበባቸው ክስ የዋስትና መብት እንማያስከለክላቸው በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጭምር መጠየቃቸውን ጠበቃው አቶ ደጀኔ ፍቃዱ አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 30 ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቶ ደጀኔ ጣፋ ከዚህ ቀደም በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ጠበቃቸው አቶ ደኔ ፍቃዱ መናገራቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ ለ8 ቀናት በኤካ ኮተቤ ከቆዩ በኋላ ሐምሌ 23 ቀድሞ ታስረው ወደነበረበት እስር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤት አቶ ደጀኔ በኮሮናቫይረስ ስለመያዛቸው እንዲያረጋግጥ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታልን ሐምሌ 20 2012 ዓ.ም. በነበረው ችሎት ጠይቆ ነበር። ሆስፒታሉም በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ፤ ሆስፒታሉ በቫይረሱ ተይዘው የሚመጡ ሰዎችን ማከም እንጂ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደማያከናውን ለፍርድ ቤት ማሳወቁን ጠበቃው አቶ ደጀኔ ፍቃዱ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

አቶ ደጀኔ ጣፍ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ምንም አይነት የህመም ምልክት እንደማይታይባቸው፤ ለፍርድ ቤቱም ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት ምንም አይነት መድሃኒት እንዳልወሰዱ እና ከዛ በፊትም ምንም አይነት ምርመራ እንዳልተካሄደላቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱም የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ሐምሌ 30 2012 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው አቶ ደጀኔ ጣፋ እንዴት ወደ ሆስፒታሉ ሊገቡ እንደቻሉ እንዲሁም በ8 ቀናት ውስጥ እንዴት ከሆስፒታል ሊወጡ እንደቻሉ እንዲያስረዱ ሲል ትዕዛዝ አስተላልፏል።

አቶ ደጀኔ ከዚህ ቀደም በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሚገኝ እስር ቤት በፊት ታስረው ከነበሩት 13 ታሳሪዎች ጋር መልሰው ተቀላቅለው መታሰራቸው የጤና ስጋት መፍጠሩን ጠበቆች ተናግረዋል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ አቶ ደጀኔ ለብቻቸው እንዲታሰሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል ሲሉ ጠበቃቸው ተናግረዋል።


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ