የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳሕርላ አብዱላሂ ÷የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ጥንቃቄዎች እና መከላከሎች አሁን ላይ እየተቀዛቀዙ መምጣታቸውን ገልጸዋል ።
በሽታው ሌሎች አገራት ላይ እንዳደረሰው ጉዳት ባለማድረሱ ህብረተሰቡ “እኛን አያጠቃንም በማለት” የጥንቃቄ መንገዶችን ችላ በማለቱ የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይም በበዓላት ወቅት ይታይ የነበረው የህብረተሰቡ መዘናጋት፣ በህዝባዊ ሰልፎች የነበረው ከፍተኛ የጥንቃቄ ጉድለትና ግርግሮችን ተከትሎ የተፈጠረው ንክኪ ሌላው ቫይረሱን ያስፋፋው አቢይ ምክንያት ነው ብለዋል።
በበዓላቱም ሆነ በሰልፎቹ ወቅት የነበሩት እንቅስቃሴዎች አካላዊ ርቀትን ካለመጠበቃቸው በላይ እንደ ፊት ጭንብል ያሉ መከላከያ መንገዶችን ያልተተገበሩበት በመሆኑ ለቫይረሱ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋልም ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ዜጎች፣ የረጅም ርቀትና የከተማ አሽከርካሪዎች፣ የተፈናቀሉ ዜጎች፣ የስደተኛ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችና ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዲሁም አቅመ ደካማ አረጋውያን ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ ተብለው መለየታቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።
እንደ ኤች አይ ቪ፤ ደም ግፊት፣ ካንሰርና አስም የመሳሰሉ ተጓደኝ በሽታ ያለባቸው ዜጎችም ለበሽታው ተጋላጭ ተብለው ከተለዩት መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።
ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ለብቻ የሚታከሙበት ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሚገኝና ረጅም ርቀት የሚያሽከርከረክሩ ሹፌሮችንም በድንበሮች አካባቢ በየ 15 ቀኑ የመመርመር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል ።
አቅመ ደካማ አረጋውያንንና ጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ማቆያ ማዕከላት ለማስገባት ከሰራተኛና ማህበራዊ እንዲሁም ከሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በቀጣይ ከነሐሴ 1 እስከ 17 የሚደረገውን ‹‹ማንም›› የተሰኘ የምርመራ ዘመቻ ውጤትን ተከትሎ በኢኮኖሚው በኩል አገልግሎት የሚሰጡ የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ወደ ስራ እንደሚገቡም ወይዘሮ ሳሕርላ አስረድተዋል።
የበሽታውን ስርጭት በማያስፋፋ መልኩ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ ብለው ባለሙያዎች በሚሰጡት መመሪያ መሰረት ወደ ስራ የሚገቡት የአገልግሎት ዘርፎች እንደሚለዩ ነው ያስታወቁት።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ