ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ ለኮቪድ 19 የሚያደርገው ጥንቃቄ ላይ መዘናጋት በመታየቱ ጠንከር ያለ ቁጥጥር ጀምሪያለሁ ብሏል፡፡
ጣቢያችን በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ እንደተመለከተው ማስክ ሳያደርጉ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ሰዎች ተይዘው ስማቸው፣ የመኖሪያ አድራሻቸው እንዲሁም ስልካቸውን በፖሊስ እየተመዘገበ መሆኑን እና እንዲሁም መታወቂያ ሲጠየቁ አስተውሏል፡፡
ጣቢያችን ይህ የሰዎችን የስም ዝርዝር መመዝገብ ሂደት ቫይረሱን ከመከላከል አንፃር የሚኖረው አስተዋፆ ምን ያህል ነው ሲል ጠይቋል፡፡
በኮሚሽኑ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ እንደነገሩን በሀገራችን በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየእለቱ እየጨመረ ቢሆንም በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት ግን ዋጋ ያስከፍለናልና ይህ ከመሆኑ ሰዎች በቂ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እየሰራን ነው ብሏል፡፡
የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ተብለው የተቀመጡትን በተለይ ማስክ አድረገው የማይንቀሳቀሱ ሰዎችን በመመዝገብ ደጋጋሚ የሆኑትን በመከታተል በአስቸኳይ አዋጁ የተቀመጠውን ቅጣት እንደሚጣልባቸውም ነው ዋና ኢንስፔክተሩ የተናገሩት፡፡
ከዚህ ቀደም ማስክ ሳያደርጉ የሚንቃቀሱ ሰዎችን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው እንዲታሰሩ ይደረግ የነበረ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ሰዎችን ማሰር ስለማይቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ አዋጁን በተደጋጋሚ በሚጥሱት ላይ ግን እርምጃ ለመወስድ አሰራሩ መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመሪያ ወይም ትዕዛዝን ሆን ብሎ የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል በአዋጁ መቀመጡ አይዘነጋም።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ