የኦፌኮ አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በዛሬው እለት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።
በዚህም አቶ በቀለ ገርባ የእርስ በእርስ ግጭት ወንጀል በማነሳሳት የተጠረጠሩ መሆናቸውን ተከትሎ መርማሪ ፖሊስ በቂ ምርመራ ማድረጉን በመግለፅ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ መክፈቱን ለችሎቱ አስረድቷል።
መርማሪ ፖሊስ አቶ በቀለ በአዲስ አበባ እና በአካባቢው እንዲሁም በሻሸመኔ ባስተላለፉት ትእዛዝ በተፈጠረ ሁከትና ብጥብጥ በትራንስፖርት ዘርፉ ብቻ በመንግስት 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር፤ በግል ደግሞ 29 ነጥን 8 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የሚያመላክት 45 ገፅ ሰነድ ማሰባሰቡን ጠቅሷል።
በተጨማሪም 27 ምስክሮችን መቀበሉን የገለፀው መርማሪ ፖሊስ፥ በሻሸመኔ እና አካባቢው በተነሳው ብሄር ተኮርና ሀይማኖት ተኮር ግጭት የ32 ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ 110 ሆቴሎች መቃጠላቸውን፣ 239 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ 393 መኖሪያ ቤቶች የተዘረፉ መሆናቸውን፣ 56 ሱቆች የተቃጠሉ መሆናቸውን፥ 146 ሱቆች የተዘረፉ መሆናቸውን፣ 80 የግል ተሽከርካሪ መቃጠላቸውን፣ 1 ፋብሪካና 9 ወፍጮ ቤቶች መቃጠላቸውን 63 የግል ድርጅቶች መቃጠላቸውን፣ 42 ባጃጆች፣ 18 ሞተር ሳይክሎች የተቃጠሉ ሲሆን፥ 4 ባንኮች እና 2 የብድርና ቁጠባ ተቋማት መቃጠላቸውን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል።
እንዲሁም 1 ሺህ 128 ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።
በተጨማሪም 7 ሽጉጦች መገኘታቸውንና 2 ሽጉጦች በአቶ በቀለ ገርባ እጅ የተገኙ መሆናቸውን እና ህገ ወጥ መሆናቸውን በፎረንሲክ ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በቡራዩ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን እንዳያልፍ መንገድ እንዲዘጋ አስቀድመው ትእዛዝ መስጠታቸውን እና አስከሬን ወደ አዲስ አበባ በመመለስ 10 ቀን መስቀል አደባባይ በማቆየት፣ የሚኒሊክ ሀውልትን ለማፍረስና ቤተ መንግስት በመግባት ጥቃት ለመፈፀም እቅድ ይዘው በኦሮሚያ ብልፅግና ጽህፈት ቤት አስክሬን በሀይል ማስገባታቸውንና በዚህ ወቅትም በፀጥታ ሀይል ላይ ተኩስ በመክፈት አንዱ ህይወቱ ሲያልፍ 3 ጉዳት አንደደረሰባቸው በምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ