በመቀሌ ዓዲ-ሓቂ ተብሎ በሚታወቀዉ ትልቁ የገበያ ማእከል በደረሰ የእሳት አደጋ የወደሙት ሱቆች ቁጥር ከ520 እንደሚበልጡ የከተማዋ ፖሊስ ገለፀ፡፡ የእሳት አደጋው የደረሰው ባለፈው ቅዳሜ ለእሁድ አጥብያ ሲሆን የአደጋው መነሻ በትክክል አለመታወቁ ተጠቅሷል፡፡ የእሳት አደጋ በተከሰተበት በመቀሌዉ ትልቅ የገበያ አዳራሽ ልብስና ጫማ መሸጫ፣ የጥቅል ጨርቆች ማከፋፈያ፣ የቤትና ቢሮ እቃዎች መሸጫ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ መዉደማቸዉን ፖሊስ አረጋግጦአል።
ንብረታቸው ከወደመባቸው ነጋዴዎች መካከል አቶ ሃይላይ ገብረስላሴ በቃጠሎው እስከ 800 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ማጣታቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የመቀለ ከተማ እሳት አደጋ መከላከል ኃይል ለግብር ከፋዩ የማይመጥንና ኃላፊነቱን ያልተወጣ ብለዉታል። ቃጠሎ የደረሰበትን የገበያ ማእከል ከጎበኙ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ኢንጅነር አርአያ ግርማይ በበኩላቸዉ የከተማ አስተዳደሩና ህዝብ የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸን አመስግነዋል። በቃጠሎዉ ንብረታቸዉ የወደመባቸዉን በማቋቋም ተግባር ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ተናግረዋል። በአደጋው በንብረትና ገንዘብ ላይ ከደረሰ ቃጠሎ ውጭ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የመቀሌ ከተማ ፖሊስ ማረጋገጡን ተዘግቦል ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ