ሉክ ደንማንና አሪያን ቤሪ የተባሉ የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ ኃይል አባላት መፈንቅለ መንግሥቱን ለማካሄድ በማሴር፣ ህገ ወጥ መሳሪያ ሽያጭና በአሸባሪነት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
ግንቦት ወር ላይ አስራ ሶስት የሚሆኑ ግለሰቦች ባህር አቋርጠው ከኮሎምቢያ ወደ ቬንዙዌላ ለመግባት ሲሞክሩ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ታሬክ ዊልያም ሳብ የፍርድ ሂደቱ እንደሚቀጥልና የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥትን ያሴሩ በሙሉ ችሎት ፊት እንደሚቀርቡ ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በትዊተር ገፃቸው የተሽከርካሪዎች ምስል፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ፓስፖርቶችና መታወቂያ ፎቶዎችን አያያይዘው "አሜሪካውያኑ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች፤ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት ማቀናበራቸውን አምነዋል" ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በተደጋጋሚ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከስልጣን ሊገለብጧቸው እንደሚያሴሩና ሃገራቸውንም ለመውረር እንደሚያቅዱ ሲናገሩ ይሰማሉ።
ዶናልድ ትራምፕ የሶሻሊስት መሪውን ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ለአመታት ቢቃወሙም አሜሪካ አልተሳተፈችም ሲሉ ውንጀላውን ውድቅ አድርገውታል።
አሜሪካ የተቃዋሚ መሪውን ጁዋን ጓይዶን የምትደግፍ ሲሆን ዕውቅናም የምሰጠው መሪ ነው ትላለች።
ሉክ ደንማንና ቤሪ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ለመጣል መፈንቅለ መንግሥት የማካሄዳቸውን ኑዛዜ የቬንዙዌላው ቴሌቪዥን ከጥቂት ወራት በፊት አሳይቷል።
"ዘመቻ ጌድዮን" ተብሎ በተጠራው የመፈንቅለ መንግሥት ዘመቻም መሳተፋቸውንና ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን መግደል ወይም አፍኖ ወደ አሜሪካ የመውሰድ ተልዕኮም እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
ሉክ ደንማን ለመፈንቅለ መንግሥቱ የሚሆኑ ቬንዙዌላውያንን እንዲመለምልና ወደ ኮሎምቢያ ወስዶ ስልጠና እንዲሰጣቸው ትእዛዝ ተሰጥቶኛል ብሏል።
በመቀጠልም የሃገሪቱን አየር መንገድ በቁጥጥራቸው ስር እንዲያውሉና ፕሬዚዳንቱም ተይዘው ከሃገር እንዲወጡ አቅጣጫ መሰጠቱን ጠቁሟል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ