"ክርስቲያኖች በሙሉ የኮሮናቫይረስ በሽታ አይዛቸውም" ብለው የሰበኩት ካናዳዊ ፓስተር በማይናማር ለእስር ተዳረጉ። ፓስተሩ ከሦስት ወር እስራት በተጨማሪ በእስርም ከባድ ሥራ እንዲሰሩ ተወስኖባቸዋል።
ዴቪድ ሊህ የተባሉት ካናዳዊው ፓስተር ያንጎን በተባለው ስፍራ ከፍተኛ ህዝብ ሰብስበው በመስበካቸውም ማይናማር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ያወጣችውን መመሪያ ጥሰዋልም ተብለዋል። ጉባኤውን ያደረጉት ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።
ከጉባኤው በኋላም እሳቸውን ጨምሮ 20 ተሳታፊዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን በማይናማር ላለው የበሽታው ስርጭትም ይህ ጉባኤ ዋነኛ መንስኤ ነው ተብሏል።
ጉባኤውን ከማካሄዳቸው በተጨማሪ ሃሰተኛ ነገር በመስበካቸውም ብዙዎችን አስቆጥቷል።
"ልባችሁ ውስጥ ክርስቶስ ካለ በሽታው አይዛችሁም" በማለትም በጉባኤው ላይ ተናግረዋል።
የ43 አመቱ ሰባኪ ትውልዳቸው ማይናማር ሲሆን በዜግነታቸውም ካናዳዊ ናቸው።
በማይናማር በአሁኑ ወቅት 357 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ስድስት ሰዎችም እንደሞቱ ከጆንስ ሆፕኪንስ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ