Ads Here

ሐሙስ 6 ኦገስት 2020

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቶ ጃዋር መሀመድና እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቤ ህግ የቅደመ ምርመራ ምስክሮችን እንዲያሰማ ብይን ሰጠ።


አቶ ጃዋር መሀመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሐምዛ አዳነን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች በዛሬው እለት በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጃዋርን ጨምሮ አጠቃላይ 14 ተጠርጣሪዎች አቶ ጃዋር መሃመድ በሚል መዝገብ በመዝገብ ቁጥር 215585 ላይ የቅድመ ምርመራ መዝገብ የከፈተ ሲሆን፥ በዚህ መዝገብ ላይ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል የተጠረጠረ ጋዜጠኛም ተካቷል።

አቃቤ ህግ አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በ14ቱም ተጠርጣሪዎች ላይ በመዝገብ ቁጥር 215585 የቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግባቸው ጠይቋል።

በተጨማሪም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዚህ መዝገብ ላይ በአጠቃላይ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ 15 ምስክሮች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን፤ እንዲሁም 5 ምስክሮች ደግሞ ከመጋረጃ በስተጀርባ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲል አቤቱታ አቅርቧል።

በተጨማሪም በዝግ ችሎት ምስክሮቹ ቃላቸውን እንዲሰጡም ጠይቋል።
የሁሉም ተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው አቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታ ላይ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።

በዚህም በዝግ ችሎት ተብሎ ለቀረበው አቤቱታ በግልፅ ችሎች ምስክሮቹ እንዲሰሙ እንደሚፈልጉ እና አቃቤ ህግ የሚያቀርባቸው ምስክሮች ጭብጥ ለመከላከል እንደሚያመች እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

እንዲሁም ምስክሮቹ ከመጋረጃ በስተጀርባ የምስክርነት ቃል መስጠት እንደሌለባቸው እና ስም ዝርዝራቸውም ተለይቶ ተሰጥቷቸው አውቀዋቸው የምስክርነት ቃላቸውን ሊሰጡ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ክሱ ስልጣን ባለው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚቀርብ መሆኑን ተከትሎ የቀዳሚ ምርመራ የምስክር ቃልም ለክሱ መከላከል እንዲያስችላቸው አስቀድመው ሊያውቁት እንደሚገባም በመቃወሚያዎችን አንስተዋል።

ተጠርጣሪ አቶ በቀለ ገርባ፥ “የማስመዘግበው አቤቱታ አለኝ፤ ሀሳቤን ፍርድ ቤቱ ይቀበለኝ” ያሉ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ “በጠበቆቻችሁ በኩል በቂ ሀሳብ ተነስቷል” ሲል አልተቀበላቸውም።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ብይን ሰጥቷል።

በተለይም በስነ ስርዓት ህጉ መሰረት የቀረበው የቅድመ ምርመራ የአቃቤ ህግ ምስክሮች በዝግ ችሎት ቃላቸው እንደሚሰማ እና ይህም ክስ ከመመስረቱ በፊት የሚደረግ የቅድመ ምርመራ በዝግ ችሎት እንደሚሆን አብራርቷል።

የምስክሮችን ዝርዝር እና ጭብጥ ጉዳይ ይሰጠን ተብሎ በቀረበ መቃወሚያ ላይም ለደህንነታቸው ታሳቢ ተደርጎ እንደማይሰጥና አምስቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮችም
ከመጋረጃ በስተጀርባ ቃላቸውን እንዲሰጡ ብይን ሰጥቷል።

የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በቅድመ ምርመራ መዝገቡ ላይ የምስክሮች ቃል እንዲሰማ ለነሃሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ