የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኮምቤን ጨምሮ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ በመከላከያ ሰራዊት መያዛቸው ተሰማ። ከዎላይታ ሶዶ የአል ዐይን ምንጮቻችን እንዳረጋገጡት አመራሮቹ ስብሰባ ላይ ከነበሩበት የተያዙ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በከተማው መጠነኛ ሁከት ተከስቷል።
የዞኑ አመራሮች ክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከፌዴራል እና ከደቡብ ክልል መንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል። የዞኑ ክልል የመሆን ጥያቄ በደቡብ ክልል መንግስት ተገቢው ምላሽ አልተሰጠውም በሚል ተቃውሞ በክልሉ ምክር ቤት የዞኑ ተወካዮች ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ራሳቸውን ካገለሉ ከ6 በላይ ሳምንታት ተቆጥረዋል። የዞኑ ተወካዮች ወደ ም/ቤት እንዲመለሱ በክልሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ እስካሁን አልተቀበሉም። የዎላይታ ዞን ምክር ቤት በራሱ ጊዜ ዞኑን በክልል ለማደራጀት ወስኖ ይህን ስራ የሚያስፈጽም ምክር ቤት ማቋቋሙ ይታወሳል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደቡብ ክልል የዞንና የወረዳ አመራሮችን ሰብስበው ከአደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የክልሉን ህዝብ ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲያስቆሙ አሳስበዋል። የዞንና የወረዳ የፖለቲካ ስራዎች በአክቲቪስቶች መጠለፋቸውንም በመግለፅ አመራሩ ከጽንፈኛ እና ህገወጥ አካሄድ ካልተመለሰ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል። የክልል ጥያቄዎች የጸብ ምንጭ መሆን እንደሌለባቸው እና ጥያቄዎቹ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ምላሽ እንደሚያገኙ ስምምነት መደረሱንም አስታውሰዋል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ