Ads Here

ሰኞ 10 ኦገስት 2020

በዎላይታ ዞን በተፈጠረው አለመረጋጋት የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ

 

በዎላይታ ዞን በተፈጠረው አለመረጋጋት የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ

በትናንትናው ዕለት የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እና አክቲቪስቶችን ጨምሮ 26 ሰዎች መታሰራቸውን ተከትሎ በዞኑ በተለይም በሶዶ ከተማ በተከሰተው ሁከት በትንሹ የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን አል ዐይን ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

አንድ የዞኑ ባለስልጣን ለአል ዐይን በስልክ እንዳረጋገጡት በሶዶ ከተማ ትናንት ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ሰልፈኞ ላይ በፀጥታ ሀይሎች በተወሰደ እርምጃ የ4 ሰዎች ህይወት አልፏል። በዛሬው ዕለትም የ2 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ተናግረዋል። በቦዲቲ ከተማም እን ዲሁ 4 ሰዎች መገደላቸውን እንዳረጋገጡ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ባለስልጣን ተናግረዋል። የሟቾቹ ቂጥር ሊጨምር እንደሚችልም ነው የገለፁት።

ከሞቱት በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውንም ገልፀዋል።

በደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በተሰጠ መግለጫ በተፈጠረው ሁከት አንድ ሰው ብቻ እንደተገደለ ነው የተገለፀው።

በዛሬው ዕለትም የተለያዩ አመራሮች እና ሌሎች ተፈላጊ ግለሰቦች እየታደኑ በመያዝ ላይ እንደሚኙ አል ዐይን ከምንጮቹ አረጋግጧል።

በዞኑ የተለያዩ ከተሞች የተነሳው ሁከት ዛሬ ከሰዓት ላይ የመረጋጋት ባህሪ በማሳየት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

የሶዶ እና ሌሎች ሁከት የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ጎዳና ወጥተው ከፖሊስ ጋር የተጋጩት ሰልፈኞች አሁን ላይ ወደ ቤታቸው ስለመመለሳቸው ከተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው የዐይን እማኞች ገልፀዋል። 

ይሁን እንጂ ወደ ዎላይታ ዞን መግባትም ሆነ መውጣት እንደማይቻል አስተያየታቸውን የሰጡን እማኞች ፣ በዞኑ እንደሌለ ተናግረዋል። በሶዶ ከተማ አሁንም አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጾች እንደሚሰሙም የደረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ከ2 ሳምንታት በፊት በስም የተለዩ ግለሰቦችን ቤትና ንብረት ለማቃጠል እና ለማውደም የታቀደ እንቅስቃሴ እንደነበር አል ዐይን ያነጋገራቸው ግለሰቦች የገለጹ ሲሆን ድርጊቱ ሊፈጸም ከተያዘለት ጊዜ ከሰዓታት በፊት ለመንግሥት ጥቆማ በመሰጠቱ የጸጥታ አካላት በመግባታቸው ዕቅዱ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል። ትናንት ተፈጥሮ እስከ አሁን በዘለቀው ሁከት ብሔር ተኮር ጥቃት እና ንብረት የማቃጠል ድርጊት እንዳይፈጸም ወጣቶች ተደራጅተው ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር ምንጮቻችን ገልፀዋል።

የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በተመለከተ ትናንት መግለጫ የሰጠው የደቡብ የክል መንግስት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ፣ አመራሮቹ በአካባቢው ግጭት ለመቀስቀስ በተደራጀ መንገድ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውቋል።

በምክትል ር/መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አለማየሁ ባውዲ እንዳሉት የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የተለያዩ ህገወጥ አደረጃጀቶችን ፈጥረው ግጭት የመቀስቀስ ፍላጎታቸውን እንዲያስፈጽሙ እያደረጉ ነበር። በፓርቲም በግለሰብም ደረጃ ሀገር ለማፍረስ ከሚን ቀሳቀሱ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ በማለት አቶ አለማየሁ ከገለጿቸው የህወኃት እና የኦነግ ሸኔ አካላት ጋር በድብቅ ሰው እየላኩ ስብሰባ እንደሚያደርጉ እና ተልዕኮ እንደሚቀበሉም በመግለጫቸው ይፋ አድርገዋል። ለዚህም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት መረጃዎች ተገኝተዋል ነው ያሉት አቶ አለማየሁ። 

የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ በመተላለፍ ህገወጥ ስብሰባዎችንና ሰልፎችን ማድረጋቸውም ተገልጿል። ህብረተሰቡ የሰጡትን አመራር ቢቀበላቸው በአካባቢው ግጭቶች ይፈጠሩ እንደነበር አቶ አለማየሁ ተናግረዋል። ከህገ መንግሥት ውጭ በመንቀሳቀስ ክልሉን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን በመግለፅ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም በእኩይ ድርጊታቸው መቀጠሉን ምረጣቸውንም አቶ አለማየሁ አብራርተዋል።

የዞኑ አመራሮች ከክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከፌዴራል እና ከደቡብ ክልል መንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል። የዞኑ ክልል የመሆን ጥያቄ በደቡብ ክልል መንግስት ተገቢው ምላሽ አልተሰጠውም በሚል ተቃውሞ በክልሉ ምክር ቤት የዞኑ ተወካዮች ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ካገለሉ ከ6 በላይ ሳምንታት ተቆጥረዋል። የዞኑ ተወካዮች ወደ ም/ቤት እንዲመለሱ በክልሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ እስካሁን አልተቀበሉም። የዎላይታ ዞን ምክር ቤት በራሱ ጊዜ ዞኑን በክልል ለማደራጀት ወስኖ ይህን ስራ የሚያስፈጽም ምክር ቤት ማቋቋሙ ይታወሳል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደቡብ ክልል የዞንና የወረዳ አመራሮችን ሰብስበው ከአደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የክልሉን ህዝብ ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲያስቆሙ አሳስበዋል። የዞንና የወረዳ የፖለቲካ ስራዎች በአክቲቪስቶች መጠለፋቸውንም በመግለፅ አመራሩ ከጽንፈኛ እና ህገወጥ አካሄድ ካልተመለሰ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል። የክልል ጥያቄዎች የጸብ ምንጭ መሆን እንደሌለባቸው እና ጥያቄዎቹ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ምላሽ እንደሚያገኙ ስምምነት መደረሱንም አስታውሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጥረት የነገሰባቸውን የዎላይታ ፣ የጋሞ እና የጎፋ ዞን አመራሮችን ከቀናት በፊት በተናጥል ማወያየታቸውም ይታወቃል።

2 አስተያየቶች:

  1. 04/12/2012 ዓ.ም
    ከምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    ምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ምክክር ፓርቲ) ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም
    በአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት እውቅና ያገኘ ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲው በ 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ የሚታገልባቸው
    የምርጫ ማኒፌስቶ 132 ገፅ የያዘ እና 70 አንቀፆች ያሉትን በማዘጋጀት ከነሀሴ 02 እስከ ነሀሴ 04 ቀን
    2012 ዓ.ም (ለ3 ተከታታይ ቀናት) ከፍተኛ አመራሩ ውይይት አድርጎ ማሻሻያዎችን በማድረግ አፅድቋል፡፡
    በመሆኑም፡-
    1. ማኒፌስቶው የአባሎችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግና አባላት እንዲታገሉበት የውክልና አሰራርንና ምርጫን እንደዋነኛ
    የአሰራር ስልት በመውሰድ የፓርቲው አባሎች አላማና ፅናት እንዲያድግ፣በአጠቃላይ ማኒፌስቶው የፓርቲው እንቅስቃሴ
    ቀልጣፋ፣አስተማማኝና አመርቂ እንዲሆን እውቀትን፣ገንዘብንና ጊዜን ባቀናጀ መልኩ አባሎች ተሳትፎዓቸውን
    እንዲያጠናክሩና እንዲያጎለብቱ ብሎም ይህ የአቋም መታገያ ማኒፌስቶ በሕዝቡ ውስጥ እንዲሰርጽ ዋና መሳሪያ ሆኖ
    እንዲያገለግል እንሰራለን፣
    2. ፓርቲው የዜጎችን ነፃነት ለማስከበር የሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል ሲሆን ፅንሰ ሀሳቡንና
    ፍልስፍናውን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የሕዝብን ፍላጐት መሠረት ያደረገ ጠቃሚ እሴቶችን በመውሰድና ከሚቀርፃቸው
    ፖሊሲዎች አንፃር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ላይ መሠረት በማድረግ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን ያደርጋል፡፡
    3. ምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የመራጩን ውክልና ለማግኘት ለምርጫ ቅስቀሳ ፓርቲው የሚጠቀምበት
    ሲሆን 6ኛ ሀገራዊ ብሔራዊ ምርጫን ካሸነፈ ወይም ጥምር መንግስትን ለመመስረት የሚያስችለውን ወንበር በፌዴራል
    ደረጃ ካገኘ በ6 ወራት ጊዜ ውሰጥ በማኒፌስቶው የተዘረዘሩትን የትኩረት አቅጣጫዎች ለመተግበር ይንቀሳቀሳል፡፡
    4. ምክክር ፓርቲ በሰላማዊ ትግል ምርጫ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ለመፍጠር፣ ልማትን ለማረጋገጥ
    የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ለመደገፍ፣ ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ ማህበራዊ ፖሊሲን ሥራ ላይ ለማዋል፣ የሀገሪቱን
    ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚደረግ ወሳኝ ውሣኔ የሚተገበርባቸው ሠነድ በመሆኑ
    የፓርቲው አመራሮችና አባላት ለተግባራዊነቱ እንታገላለን፡፡
    5. በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግስት የተሸከማቸው ተግዳሮቶችን ፓርቲው ነቅሶ ያወጣበት ማኒፌስቶ በመሆኑ ሕገ
    መንግስቱ ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ በሆነ መልኩ በአዲስ መልክ ተቀርፆ ሊጻፍ ይገባል ፣ ለተግባራዊነቱ
    እንንቀሳቀሳለን፣
    6. በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግ፣ አንዱ ከሣሽ ሌላው ተከሳሽ ሆኖ በመካሰስ ላይ የማናተኩር
    መሆኑንና የቂም፣ የበቀልና የመጠላለፍ ፖለቲካ ሊያበቃ ይገባል ብለን እናምናለን፣
    7. ብሔራዊ የአንድነት እርቅ ኮሚሽን ተቋቁሞ ብሔራዊ እርቅ በሀገራችን እንዲፈጠር ማድረግ ከቻልን በሕዝብ
    የተመረጠ፣ለሕዝብ የቆመ መንግስት በመመስረት የዜጎችን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በመምራት ለድል ማብቃትና
    የዜጎችን ሰላምና የኑሮ ዋስትና ማረጋገጥ ይቻላል ብሎ ምክክር ፓርቲ ያምናል፡፡ለተግባራዊነቱ ይንቀሳቀሳል፡፡
    8. ምክክር ፓርቲ ሁሉም ሰዎች በተፈጥሯቸው እኩል በመሆናቸው ኢትዮጵያዊያን በዘር፣ በቀለም፣ በኃይማኖት
    በአመለካከት ወዘተ…ላይ የተመሠረተ ግጭት ውስጥ ሊገቡ አይገባም፣ ሊያጋጩን የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድብቅ
    አጀንዳ ልንቀበል አይገባም፣ በግልጽ ልንታገላቸውም ይገባል፣
    9. ምክክር ፓርቲ የጀመረውን ትግል ከግቡ ለማድረስ የመረጠው ስልት ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ነው፡፡ ወደ
    ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሸጋገሪያው ዋነኛው ድልድይ እርቅ መፍጠር ወይም ግለሰቦች፣ ሕዝቦችም ሆነ አገሮች ያለፈና
    የማይለውጡት ታሪካቸውን ተቀብለው ከዛ ጋር የተቆራኙ ችግሮችን በመፍታት ላይ የሚያተኩሩበት ሂደት ለመፍጠር
    እንሰራለን፣
    10. በጠመንጃ አፈ ሙዝ የስርዓት ለውጥ የሚያደርጉ ሀይሎች ወደ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ
    ጥሪያችንን እናቀርባለን፣
    11. ከጥምር ጎሳ የተወለዱ ከ 43 ሚሊዮን ዜጎች በላይ በሀገራችን ያሉ በመሆኑና የአዲስ አበባ እና ሌሎች
    ትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ ሕዝቦች በፌዴሬሽን ም/ቤት ውክልና የላቸውም፤ በመሆኑም ውክልና እንዲኖራቸው
    ለተግባራዊነቱ ፓርቲያችን ምክክር ይታገላል፡፡
    12. በመሬት አስተዳደር በመንግስት ገቢ አሰባሰብ በትላልቅ የመንግስት ግዥና ሽያጭ እንዲሁም በፍትሕ አስተዳደር
    ዙሪያ ሙስና ለመከላከልና ለመዋጋት መንግስት እቅድና ትኩረት ሰጥቼ ውጤት አምጥተናል ቢልም በርካቶታ የመንግስት
    ተቋማት በከፍተኛ የሙስና ተግባራት መዘፈቃቸው የፌዴራል ኦዲተር ሪፖርት ተገንዝበናል፣በመሆኑም መንግስት ትኩረት
    ሰጥቶ ችግሩን ከስሩ እንዲቀርፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን፣
    13. ኢትዮጵያ ያላትን ሀገራዊ ሀብቶች መሠረት በማድረግ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት
    ያላት በመሆኑ በወንዙ ተጠቃሚነት ላይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የትብብር ዘላቂ መዓቀፍ እንዲኖር ፣በመንግስት
    ድንበር ተሸጋሪ ወንዞቻችንን በሚመለከት ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር የሚያስችሉ ስምምነቶች እንዲኖሩ
    የሚደረገውን ጥረት እንደግፋል፣
    14. የአባይ ወንዝ የስምምነት ማዕቀፍ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ብቻ የሚደረግ ውይይት ሌሎች ሀገራትን
    ሊያስኮርፍ ስለሚችል የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ ወደ ስምምነት ማዕቀፉ ሊገቡ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡
    ለተግባራዊነቱ መንግስት እንዲሰራ ጥሪ እናቀርባለን ፣
    15. በለውጡ መንግስት ውስጥ ተሰግስገው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚያስፈፅሙትን እንደ ጥፋታቸው መጠን ለሕግ
    እንዲቀርቡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

    ድል ለአንድነት ሀይል !
    ዘረኝነትን እናወግዛለን !

    ነሀሴ 04 ቀን 2012 ዓ.ም

    ምክክር ፓርቲ

    ምላሽ ይስጡሰርዝ