በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ ጥይት ተኩሶ በመግደል ወንጀል የተጠረጠረው አቶ ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል አረጋገጠ።
ተጠርጣሪው “ይህንን ተልእኮ የሰጡኝ ሰዎች ድርጊቱን መፈፀምህን በሚስጥር የማትይዝ ከሆነ በቤተሰቦችህ ላይ ጉዳት እናደርሳለን” በማለት እንዳስጠነቀቁት ለፈደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የአራዳ ምድብ፣ አንደኛ ወንጀል ችሎት ተናግሯል።
በዚህም “ለቤተሰቦቼ በቂ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና የኔም ጉዳይ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ” በማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል።
“የፀሀይ ብርሀን አግኝቼ አላውቅም፣ ካቴና ከእጄ አልወለቀም፣ ክስ እስከሚመሰረትብኝ እንኳን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር እንድቀላቀል ይደረግልኝ” በማለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቧል።
ተጠርጣሪው ባለፈው የጊዜ ቀጠሮ በዚሁ ችሎት ቀርቦ “እራሴን እንዳጠፋ ይፈቀድልኝ” ማለቱን ችሎቱ አስታውሷል። በዚያው ቀጠሮው መርማሪ ፖሊስ ካቴናው ከእጁ የማይወልቀው ተጠርጣሪው እራሱን እንዳያጠፋ ለመከላከል መሆኑንም ችሎቱ ገልጿል።
መርማሪ ፖሊስ በዛሬው ቀጠሮው ተጠርጣሪው የካቴናውን ጉዳይ ዳግም በማንሳቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚመለከተው የስራ ሀላፊ በቀጣይ ቀጠሮው ስለሁኔታው ያስረዳ ብሏል ችሎቱ።
ፖሊስ ባለፈው የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ያከናወነውን የምርመራ ስራ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በቀጣይ በተለይም በቁጥጥር ስር ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጀርባ ድርጊቱን ያቀነባበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን ለማደራጀት ከጠየቀው 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ 11 ቀን ፈቅዷል።
ፍርድ ቤቱ ውጤቱን ለመጠባበቅም ለነሀሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ