Ads Here

ቅዳሜ 8 ኦገስት 2020

የትናንቱ የኦነግ አመራሮች፣ አባላት እና የኬንያዊው ጋዜጠኛ የፍርድ ቤት ውሎ

 

ከፍተኛ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች እና አባላትን ጭምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ትናንት ዓርብ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. የሱሉልታ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ከተጠርጣሪ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ቶኩማ ዳባ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትናንት ፍርድ ቤት የቀረቡት በኮሎኔል ገመቹ አያና መዝገብ ሥር የተካተቱ 11 ተጠርጣሪዎች ናቸው። ከእነዚህም መካከል የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች እና አማካሪዎች ኮሎኔል ገመቹ አያና፣ ሽጉጥ ገለታ (ዶ/ር)፣ ሚካኤል ቦረን እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይገኙበታል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ፤ የሰው ነብስ እንዲጠፋ፣ በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ፣ መንግድ እንዲዘጋ እና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቆም አድርገዋል ሲል ጠርጥሬያቸዋለሁ ስለማለቱ ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሥማቸውን ከላይ የተጠቀሰው የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ አንድ ወር ቢያልፋቸውም፤ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን እና ከቤተሰብና ከጠበቆቻቸውም ጋር ግነኙነት እንዳልነበራቸው ጠበቃ ቶኩማ ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን አስታውቆ፤ የምርመራ መዝገቡ ተዘግቶ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ማቆያ እንዲያመሩ መጠየቁን ጠበቃ ቶኩማ አሳውቀዋል።

ፍርድ ቤቱ፤ ዐቃቤ ሕግ በ15 ቀናት ውስጥ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ እንዲመሰረት፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ግን ክስ የማይመሰረት ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ በተጠቀሰው ጊዜ ፍርድ ቤት መምጣት ሳያስፈልጋቸው ከእስር ይውጡ ብሎ በማዘዝ የመርመራ መዝገቡ መዘጋቱን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትናንቱ የፍርድ ቤት ውሎ የተጠርጣሪ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ከዚህ በፊት አግኝተው እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ በመናገር፤ ደንበኞቻቸው ተይዘው የሚገኙበት ሁኔታ መብታቸውን የሚጠብቅ አለመሆኑን እና ለችግር ተዳርገው እንደሚገኙ ለፍርድ ቤት አስረድተዋል።

በተለይ የስኳር እና ደም ግፊት ሕመሞች ተጠቂ የሆኑ ተጠርጣሪዎች የሚወስዷቸውን መድሃኒቶች ሊያገኙ አለመቻላቸውን ጠበቃው ለፍርድ ቤት ማመልከታቸውን ተናግረዋል።

ከተጠርጣሪዎች መካከል የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ኮሎኔል ገመቹ አያና ታስረው የሚገኙበት ስፍራ በቂ የጸሃይ ብርሃን እንደሌለው እንዲሁም በቂ ምግብ እያገኙ አለመሆኑን በመጥቅስ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።

ጠበቃው ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ፍርድ ቤቱ የታሳሪዎች አያያዝ መብት እንዲከበር፤ መድሃኒት የሚያስፈልጋቸውም መድሃኒት እንዲቀርብላቸው፣ ከቤተሰብ እና ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማዘዙን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ጫልቱ ታከለ ትናንት የሱሉልታ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት መቅረቧን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል። የኦነግ አባል የሆነችው ጫልቱ ታከለ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ የአራዳው ምድብ ችሎት በ4 ሺህ ብር የዋስ መብት ከእስር እንድትወጣ ካዘዘ በኋላ፤ ጫልቱ ዳግም በኦሮሚያ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውላ ወደ ሱሉልታ መወሰዷ ይታወሳል።

በትናንቱ ውሎ መርማሪ ፖሊስ ጫልቱ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀ ቢሆንም የሱሉልታ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት ግን ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ በማድረግ በከዚህ ቀደሙ የዋስትና መብት ከእስር ትውጣ በማለት ማዘዙን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌሎች በሱሉልታ ተይዘው የሚገኙት የኦነግ መካከለኛ አመራር የሆኑት ለሚ ቤኛ እና ዳዊት አብደታ በተለያዩ ምክንያቶች ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ጠበቃው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ትናንት ነሐሴ 1 2012 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ፖሊስ የጠየቀውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ኬኒያዊውን ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ጨምሮ 11 ሰዎች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር ይለቀቁ ሲል መበየኑን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አብዱለጢፍ አሜ ኤሌሞ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ ያሲን ጁማን ጨምሮ 11 ተጠርጣሪዎች ሐምሌ 29 የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቅ ከእስር ሳይለቀቁ ቆይተው ነበር።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ