የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ስንታየሁ ደበሳ እንደተናገሩት በሕክምና ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው እተደረገ ያለውን ወረርሽኙን የመከላከል ሥራን ያዳክመዋል የሚል ስጋት አለ ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጤና ባለሙያዎቹና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቹ ለኮሮናቫይረስ የተጋለጡት በሥራ ቦታቸው ላይ እያሉ ነው።
ወይዘሮ ስንታየሁ ለጤና ባለሙያዎቹ በሽታውን ለመከላከል አስፈጊ የሆኑ አቅርቦቶችን በተመለከተም አስተዳደሩ በበቂ ሁኔታ ማቅቡንና ገልጸው "እስካሁን ድረስ እጥረት የለብንም" ብለዋል።
ነገር ግን በሕክምና ተቋማቱ የሚኖሩ ንክኪዎች ባለሙያዎቹን ለቫይረሱ ማጋለጡን የሚናገሩት አስተባባሪዋ፤ ከባለሙያዎቹ ጋር በተደረገ ውይይት ለቫይረሱ የተጋለጡት በየትኛው ጊዜ እንደሆነ ለማለየት እንደሚቸገሩ ገልፀዋል።
በህክምና ተቋማቱ ያሉ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት ግን ይላሉ ባለሙያዋ "በሕክምና ሥራ ላይ እያሉ ተጋላጭ መሆናቸውን ነው" በማለት ባለሙያዎቹ እየወሰዱ ያሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የጤና ባለሙያዎቻችን በቫይረሱ እየተያዙ መምጣት ወረርሽኙን ለመከላከል የምናደርገውን ጥረት ያዳክማል" ሲሉም በአስተዳደሩ በኩል ያለውን ስጋት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቫይረሱ ከተያዙት የሕክምና ባለሙያዎች መካከል በድንገተኛ እና በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚሰሩ ነርሶችና ዶክተሮች እንደሚገኙበት በመጥቀስ፤ በዚህ ክፍል የሚሰሩት ባለሙያዎች በሥራ ባህሪያቸው ምክንያት ተጋላጭ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በድሬዳዋ እስካሁን ድረስ ስምንት ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ናሙናዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሲደረገላቸው፤ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከ500 በላይ ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸውንና 20 ያህል ሰዎች ደግሞ በዚሁ ምክንያት መሞታቸው ታውቋል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከ400 በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ማገገማቸውን የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪዋ ስንታየሁ ደበሳ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በተያያዘ ዜና በምሥራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ በሚገኙ ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ 66 ታራሚዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ተካ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በጊኒር ከተማ እና በወረዳው በሚገኙ ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ በተደረገው የኮቪድ-19 ምርመራ እነዚህ ታራሚዎች ኮሮናቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ኃላፊው ተናግረዋል።
እነዚህ ቫይረሱ የተገኘባቸው ታራሚዎች ለህክምና ወደ ሮቤ ሆስፒታል መላካቸውንም ቢቢሲ ከኃላፊው መረዳት ችሏል።
ኃላፊው በእነዚህ ፖሊስ ጣቢያዎች ታራሚዎች አካላዊ ርቀታቸውን መጠበቅ በማያስችላቸው እና ያለ ምንም ጥንቃቄ መልኩ መታሰራቸው በሽታው እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች የፀረ ተህዋሲ ርጭት ተደርጓል።
በቀላል ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችም የዋስ መብታቸው ተጠብቆ እንዲወጡ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑንም ተናግረዋል።
ታራሚዎቹን ለመጠየቅ የሚመጡ ቤተሰቦችም በሽታውን ወደ ኅብረተሰቡ ይዘው በመሄድ ስርጭቱ ይስፋፋል የሚል ስጋት ቢኖርም እስካሁን ድረስ ከተጠረጠሩት ሰዎች ላይ በተወሰደ ናሙና ላይ በተደረገ ምርመራ የተያዘ ሰው አለመገኘቱን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን 470 ሺህ የሚጠጋ ምርመራ ተደርጎ ወደ 21 ሺህ 452 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል። ከእነዚህም መካከል በወረርሽኙ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 380 ደርሷል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ