ተጠርጣሪዎች አዲሱ ቶሎሳ፣ ደስታ ሽኩር ፣ጥላሁን ለታ፣ አበራ ሁንዴ፣ ሙስተዋሪድ አደም፣ አረፋት አቡበከር፣ አማን ቃሎ፣ ሱልጣን በድያ፣ ውቢ ቡርቃ፣ ሀቢቢ ሳፈው፣ ጉቱ ሙሊሳ፣ ሲሳይ በቀለ፣ ሮባ አዳነ እና ጉልማ ከፈና ናቸው።
እንደ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት የሟች አስከሬን ወደ አምቦ ሳይደርስ አዲስ አበባ ተመልሶ ወደ ኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ይዘው ሲገቡ የተገኙ ናቸው።
ከእነ አቶ ጃዋር ጋር በመሆን አስከሬኑ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ 1ዐ ቀን ተለቅሶ የሚኒሊክ ሐውልትን በማፍረስ ቤተመንግስቱን መቆጣጠር የሚለውን ዓላማ ሲያራምዱ የተገኙ መሆናቸውንም ጠቅሷል ፖሊስ በምርመራ መዝገቡ፡፡
ከተጠርጣሪዎች ሲሳይ በቀለ የተባለው፣ “ሟች ዘመዴ ነው ለቅሶ ልደርስ ሄጄ አስከሬኑ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ አብሬ ተመልሼ ከኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ተያዝኩ እንጂ የፈፀምኩት ጥፋት የለም፤ የዋስትና መብቴ ይጠበቅልኝ” በማለት አመልክቷል።
ሌላኛው ወቢ ቡርቃ የተባለው ተጠርጣሪ ያጠፋው ጥፋት እንደሌለ እና የዩኒቨርስቲ ተማሪ እንደመሆኑ መጠን “የነገ ተስፋዬን በማየት ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቴን ይጠብቅልኝ” ብሏል፡፡
በእስር ሆኖ በኮሮና ቫይረስ ተይዞ 15 ቀን በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሲታከም ሕመሙን ተገናዝቦ እንደ ታካሚ ሳይሆን እንደ እስረኛ ሆኖ 15 ቀኑን በመጥፎ ሁኔታ ማሳለፉንም ለችሎቱ ገልጿል።
ጠበቆችም እንዲሁ የተጠርጣሪዎች የየግል ጥፋት ተለይቶ አልተቀመጠም፣ ያጠፉት ጥፋትም የለም፤ በዚህም የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል።
የምርመራ ቡድን የሰጠውን ምላሽ ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ተፈፀመ ከተባለው ወንጀል ስፋት አንጻር የተጠየቀውን የዋስትና ጥያቄ አልተቀበለም።
የፖሊስን የምርመራ መዝገብ እየተመለከተ መሆኑን በመጥቀስ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ 12 ቀናቱን ለመጨረሻ በማለት ፈቅዷል።
ወቢ ቡርቃ የተባለው ተጠርጣሪ በኤካ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ሕመምተኛ ሁኖ የቆየበትን ሁኔታ ሆስፒታሉ በጽሁፍ እንዲያስረዳም አዝዟል።
ውጤቱን ለመጠበቅ ለነሐሴ 13 ቀን 2012 ተለዋጭ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ይዟል።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ